Thursday, December 23, 2010

deresge mariam by daniel kibrer

iw baye (ke daniel kibret)sef
ዝንጀሮ አቋረጠን ምን እንሆን ይሆን?
ከጎንደር ተነሣን፤ እኔና ሙሉቀን ዘጎንደር፡፡ አንዳንዶቹ የልደታ ምክትል መልአከ ስብሐት ይሉታል፡፡ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ስለሆነ፡፡ የምንጓዝበትን መኪና ያመቻቸልኝ የአዲስ አበባው ሙጨ ነው፡፡ ምንም እንኳን 3500 ቢያስሰክፉንም፡፡ ከጎንደር ወደ ጃናሞራ መውጫው በር ብልኮ ይባላል፡፡

መኪናችንን አስፈታትሸን እና ነዳጅ ሞልተን ከብልኮ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተነሣን፡፡ እስከ ዳባት ያለው መንገድ ከጎንደር ተራሮች አንፃር እንደሜዳ የሚቆጠር ነው፡፡ ሜዳ በሌለበት ዳገት ሜዳ ይሆናል ሲባል አልሰማችሁም፡፡

ፀሐይ እና ብርድ ለማሸነፍ ይፎካከራሉ፡፡ በመካከል እኛ ካፖርት በመልበስ እና በማሞቅ ዕንቆቅልሽ እንሠራለን፡፡ የወገራ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችውን አምባ ጊዮርጊስን አለፍናት፡፡ መኪናዋ እህም፣ እህም፣ እህም እያለች ታዘግማለች፡፡ ቻይና እዚህም አለች፡፡ ይህንን የስሜን መንገድ እንደ ጨጓራ ትገለብጠዋለች፡፡ ከጎንደር ወደ ደባርቅ የሚወስደው መንገድ በአዲስ መልኩ እየተሠራ በመሆኑ በተለዋጭ መንገድ እንፈጨዋለን፡፡

የስሜን መንገድ
ገደብዬን አለፍናት፡፡ ከጎናችን በላንድ ክሩዘር የፈረንጅ ዘር ከነ ግልገሉ እንዳትቀር የተባለ ይመስል እየጣለን ይፈስሳል፡፡ ከአዲስ አበባ 830 ኪሎ ሜትር ተጉዘን ይኼው ዳባት ላይ ተገኘን፡፡ የደጃዝማች አያሌው ብሩ ቤተ መንግሥት የሚገኘው እዚህ ነው፡፡ የስሜንን ተራሮች ለማየት የምትጓዙ ሳታዩት አትለፉ፡፡ የወረዳው መስተዳድር በከተማዋ ያሉትን የሚጎበኙ ቦታዎች በቢል ቦርድ መንገዱ ዳር መስቀሉ ያስመሰግነዋል፡፡ ለጎብኚዎች መረጃው ይጠቅማልና፡፡

በምቃራ በኩል አልፈን 830ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ደባርቅ ላይ ወረድን፡፡ ምሳ የሚበላው እዚያ ነው፡፡ የወረዳው የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ምሳ ጋበዙን፡፡ ሜዳው እዚህ ያበቃል፡፡ መንገዱም ለሁለት ይከፈላል፡፡ ወደ ሽሬ እና ወደ ጃናሞራ፡፡

http://www.blogger.com/post-create.g?blogID=5530639373142209837ሊማሊሞን ዳገት ወጣሁት በዳዴ
እንደ ዘጠኝ ወር ልጅ አርግዤህ በሆዴ

ተብሎ የተዘፈነለት የሊማሊሞ ገደል በሽሬው መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ ሊማሊሞ መንገዱን የገነባው ጣልያናዊ መሐንዲስ ስም ነው፡፡ የታደለ ጣልያን መንገድ ሠርቶ ስሙን ተክሎ ሄደ፡፡ የሊማሊሞ መንገድ ሊቀር ነው ይባላል፡፡ አሁን የሚሠራው አዲሱ የሽሬ መንገድ በሊማሊሞ በኩል አይሄድም፡፡ ቦታውን ግን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መታሰቡን ሰምቻለሁ፡፡ ሊማሊሞን ያላያችሁ ይሄኔ ነው ማየት፡፡ በኋላ የቱሪስት መዳረሻ ብቻ ከሆነ በብር መክፈላችሁ ቀርቶ በዶላር መክፈላችሁ አይቀርም፡፡ ቱሪስት በሚባ ዛባቸው የሀገራችን ቦታዎች ያለው አንዱ ችግር ሁሉንም በዶላር የማሰብ አባዜ ነው፡፡ እዚያ የምትተነፍሱትም በዶላር ነው፡፡

ከደባርቅ ወጣን፡፡ የደባርቅን ጉልት ገበያ አቋረጥናት፡፡ የጃን አሞራን መንገድ ያዝነው፡፡ ታዋቂው ስሜን ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘው በዚህ ነው፡፡ አንድ ሃያ ኪሎ ሜትር
እንደሄድን ወደ ፓርኩ ክልል ገባን፡፡ መኪናችንን እህህ ማለት ትታ፣ አዬዬ እያለች ማማረር ጀመረች፡፡ ለዝንጀሮ የተዘጋጀን ተራራ ይህች ያረጀች መኪና በምን ልቧ ትውጣው፡፡ በግራ በኩል ከሰማይ ጋር የተሳሳመው ተራራ ይታያል፡፡ በቀኝ በኩልም የርሱ መንትያ ተገትሯል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የገበሬዎች እርሻ ቢታይም አካባቢው ግን ከሰው መኖርያነት ነጻ የሆነ ይመስላል፡፡

የዝንጀሮ ማኅበር
እነሆ ጭላዳ ዝንጀሮ ማኅበር ሲጠጣ አገኘነው፡፡ ዕድር ይሆን ዕቁብ አላወቅንም እንጂ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ጭላዳ ማኅበር ይጠጣላችኋል፡፡ አንዳንዶቹ መሬት ይጭራሉ፤ ሌሎቹ ይቃለዳሉ፤ ሌሎቹም ልጆቻቸውን ይቀምላሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ልጆቻቸውን አዝለዋል፡፡ የማኅበሩ ሙሴ የሚመስለው ግመሬ ዝንጀሮ መሐል ላይ ገብቶ ጎምለል ጎምለል ይላል፡፡

እኛን ሲያዩ ወደ ዳገታቸው ሸሸት ሸሸት አሉ፡፡

ከእነርሱ እልፍ ብሎ ለቱሪስቶች የተዘጋጁ ሎጆች አሉ፡፡ እዚያው ሲጎበኙ ውሎ፣ እዚ ያው አምሽቶ እዚያው ማደር ይቻላል፡፡

መኪናችን እያማጠች እያ እየተመሰጥን ጉዞ ቀጠልን፡፡ እነሆ ዋልያ፡፡ ሁለት ጓደኛሞች የት እንደቆዩ አይታወቅም ከተራራው ላይ እየተጫወቱ ወረዱ፡፡ እኛ ስናያቸው መንገዱን አቋርጠው ፈረጠጡ፡፡ ካሜራዬ ግን አንዱን ሲዘል ያዘችው፡፡ ዋልያን ከነ ሕይወቱ ሳየው የመጀመርያዬ ነው፡፡
ዋልያዋን አየናት

ስሜን ተራራ በኢትዮጵያ ታሪክ ዝናው ከፍ ያለ ነው፡፡ የጎንደር ሥርወ መንግሥት መሥራች ዐፄ ሠርጸ ድንግል ከአካባቢው ፈላሾች ጋር ብዙ ውጊያዎች

አድርገውበታል፡፡ የጦር አዛዣቸው ዮናኤል በ1572 ዓም ረዳኢ ከተባለው የፈላሾች መሪ ጋር የተዋጋው እዚህ ቦታ ነው፡፡ በኋላም በ1579 ዓም ጎሼን ወግቶበታል፡፡
ታኅሣሥ 6 ቀን አባ ንዋይ የተባሉ ከወላይታ የመጡ ካህን ታቦተ ኢየሱስን ይዘው በድንኳን የቀደሱት እዚህ ቦታ ነበር፡፡ ንጉሡ ጎሼን ሲያሸንፈውም በዚሁ ቦታ ታቦተ ኢየሱስ አምባ መሸኻ ወደተባለው አምባ ወጥተው ዘምረዋል፡፡ ይኼው ታቦት ነው በኋላ ዘመን ጎንደር ላይ ተተክሎ አደባባይ ኢየሱስ የተባለው፡፡ ታቦቱ የመጣው ከወላይታ መሆኑን የዐፄ ሠርፀ ድንግል ዜና መዋዕል ይናገራል፡፡ እንግዲህ ጎንደሬም ወላይቴ፣ ወላይቴም ጎንደሬ ነው ማለት ነው፡፡ ስለ ስሜን እና ስሜነኞች  በሚገባ ማወቅ የፈለገ «ስሜን እና ስሜነኞች» የተሰኘውን የጋዜጠኛ ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር ጽሑፍ ቢያነብ  መልካም ነው፡፡ ጽሑፉ በኅብረ ነገር የመጀመርያ መጽሐፉ ላይ ይገኛል፡፡
የስሜን ተራሮች

በግራ በኩል በማዶ የጠመጠመ የሰሜን ካህን መስሎ ራስ ደጀን ይታያል፡፡ እኔ ወደዚያ ለመድረስ ጊዜ አልነበረኝምና በሩቁ ተሳልሜው አለፍኩ፡፡
የቧሂት ተራራ
አሁን ቧሂትን እያለፍነው ነው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ከደጃች ውቤ ጦር ጋር ተዋግተው ያሸነፉበት አስቸጋሪው ተራራ ነው ቧሂት፡፡ የደጃች ውቤ ጦር በጃን አሞራ ሲከትም ደጃዝማች ካሣ «ስሜን ስሜን እነግርሃለሁ» ብለው ነበር አሉ ወታደር ያስከተቱት፡፡ እንዳሉትም ቧሂት ላይ ተዋግተው ስማቸውን ስሜን ላይ ነገሩት፡፡
ከቧሂት ወደዚያ የተሻለ ሜዳ ነው፡፡ ሜዳ ከተባለ፡፡ መኪናችንም እዬዬ ከማለት እምምም ወደማለት ተሸጋግራለች፡፡ ከፊት ለፊታችን የጃን አሞራ ወረዳ ዋና ከተማ መካነ ብርሃን ትታየናለች፡፡ ወደ እርሷ ከመግባታችን በፊት «ድል ተራራ» የተባለው የደጃች ውቤ ተራራ ይገኛል፡፡ መሣርያቸውን አከማችተውበት የነበረው ቦታ
ዋልያ ከነ ቤተሰቡ
መሆን አለበት፡፡

መካነ ብርሃን ገባን፡፡ ከቀኑ አሥር ሰዓት ሆኗል፡፡ የዚህ ሀገር ፀሐይ ደግሞ ካልገባሁ እያለች ነው፡፡ መብራት እነደ ልብ ባለበት ከተማ ቀስ ብላ የምትገባው ፀሐይ እዚህ ምን ልሁን ብላ ትቸኩላለች፡፡ «ሰው ሆይ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ» ለተባለው ቃል የሰነድ ማስረጃ መስለናል፡፡ አሁን ተሠርተን ገና ጭቃችን የደረቀ ይመስላል፡፡

እኛና ውኃ ተገናኝተን ስንለቃለቅ አስራ አንድ ሰዓት ሆነ፡፡ በመካነ ብርሃን ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የሠርክ ጉባኤ ለመካፈል ወደዚያው ሄድን፡፡ እንዲህ ዓይነት የሠርክ ጉባኤ ካየሁ ብዙ ዘመን ሆኖኛል፡፡ ከአንድ ትልቅ ዋርካ ሥር በተጋደሙ እንጨቶች ምእመናኑ ተሰብስበዋል፡፡ እዚያው እየተማርን እዚያው መሸ፡፡

የመካነ ብርሃን ኪዳነ ምሕረት የሠርክ ጉባኤ
ብሉ ነገ እንገናኝ፡፡ ደኅና እደሩ፡፡


*
በደረስጌ በር አጠገብ ያሉት እድሜ ጠገብ ዛፎች

 
ብርዳማው የመካነ ብርሃን ሌሊት አለፈ፡፡ ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ተነሣን፡፡ የወረዳው የባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ባለሞያ የሆነው አደራጀው አካባቢውን የሚጎበኙትን ሁሉ ከቡና በሚመረጠው ፈገግታ ለማስተናገድ ያለው ዝግጁነት ያስቀናል፡፡ እርሱ መካነ ብርሃን ላይ ባይኖር ኖሮ ጉብኝታችን ሁሉ ውኃ ይበላው ነበር፡፡

የደረስጌ ማርያም ካህናት በግብርና ሥራ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡ ክህነትን እንደ ሥራ ማየትኮ በቅርብ ዘመን የመጣ ጠባይ ነው፡፡ ቀደምቶቻችን እያረሱ የሚቀድሱ እና የሚያስተምሩ ነበሩ፡፡

*
  ደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን


*
የቤተ ክርስቲያኑ ዓምደ ወርቅ


ቤተ ክርስቲያኗ ከአንድ ኮረብታ ግርጌ ትገኛለች፡፡ ዙርያዋ በኖራ በተመረገ የድንጋይ ግንብ ታጥሯል፡፡ የግቢው ውስጥ በጥንታውያን ዛፎች የተሞላ ነው፡፡ በሩ እንደ ጎንደር ዘመን በሮች በሰቀላ የተሠራ ነው፡፡ ከበሩ በስተ ግራ በኩል ታቦት ሲወጣ በሚያርፍበት ቦታ ላይ ከመቶ ዓመታት በላይ የሆናቸው የግራር ዛፎች ለታሪክ ታዛቢነት ቆመዋል፡፡
 ገባን፡፡
*
            ከወርቅ የተሠራው የደረስጌ ጉልላት


ቤተ መቅደሱ ክብ ሆኖ አናቱ ላይ የወርቅ ጉልላት አለው፡፡ በሮቹ እስከ ሦስት ሜትር በሚደርሱ ግዙፍ ግንዲላዎች የተሠሩ ናቸው፡፡ የመቅደሱ ወለል ከቅርቀሃ እና ከጠፈር በተሠራ አቴና የተሞላ ነው፡፡ አቴና በጥንቱ የቤት አሠራር ጥበባችን ወለሉን ለማልበስ እንጠቀምበት የነበረ ዘዴ ነው፡፡


*
     የቤተ ክርስቲያኑ ጥንታዊ ኮርኒስ፣
     በልዩ የእጅ ጥበብ የታነፀ

ደረስጌ ጽርሐ ጽዮን ማርያም ትክሏ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን መሆንዋን የደብሩ ሽማግሌዎች ይገልጣሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ያለውን ቤተ መቅደስ አሠርተው የደበሯት እና ዛሬ ያላትን ክብር የሰጧት በ1810 ዓም ደጃዝማች ውቤ ናቸው፡፡
*
እንጨቱ ተፈልፍሎ ልዩ ልዩ ዲዛይን
የወጣለት የደረስጌ መስኮት


ደጃዝማች ውቤ ትግራይን እና ስሜንን ሲገዙ ዋና መናኸርያቸውን ደረስጌ ላይ አድርገው ነበር፡፡ በዚያ ቦታ ላይ ቤተ መንግሥት እና የመሣርያ ግምጃ ቤት ነበራቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋን ለማሠራት ከሀገር ውስጥ እና ከባሕር ማዶ ዕውቅ መሐንዲሶችን አሰባስበው ነበር፡፡ ከውጭ ከመጡት መካከል ጀርመናዊው ዶክተር ዊልሔለም ሺምበር ይጠቀሳል፡፡
  የደብሩ ክልል ሦስት ጋሻ መሬት ሲሆን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በሁለት ቅጽር እና በዐጸድ የተከበበ ነው፡፡ የመጀመርያው ቅጽር በጎንደር ከተማ እንደሚገኘው የዐፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት በዕንቁላል ቅርጽ የተገነባ ግንብ ይገኝበታል፡፡
*
ከመቶ ዓመት በላይ ያገለገለው የዘይት መቅረዝ


ወደ ቤተ መቅደሱ ስትዘልቁ ደጃዝማች ውቤ ያስሳሉትን ሥዕል ታገኛላችሁ፡፡ የቤተ መቅደሱ በር እና መስኮት ለእያንዳንዱ እንጨት ተፈልፍሎ ጌጥ እየወጣለት የተሠራ ነው፡፡ ያንን እንጨት ፈልፍሎ በላዩ ላይ ከመቶ ዓመት በላይ የሚዘልቅ ጌጥ የሚሠ ራው ማሽን የት ሄደብን? ከበሩ ግራ እና ቀኝ ሁለት ነጋሪቶች አሉ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ሲነግሡ ያስጎሰሟቸው ይሆኑ ይሆን?

*
        የደረስጌ መግቢያ በር


በዚያ ዘመን የተሠራው ለማኅሌት እና ቅዳሴ ጊዜ መብራት ይሰጥ የነበረው የዘይት መቅረዝ ዛሬም ለታሪክ ይገኛል፡፡

*
ዐፄ ቴዎድሮስ የነገሡት በዚህ ነጋሪት ይሆን?
የተቀመጠበት ወለል ነው አቴና የሚባለው


*
    አቡነ ሰላማ እና የግብጹ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ፣
         በደረስጌው ሰዓሊ ዓይን

ከበስተ ጀርባ ራሱን በቻለ  ጠባብ ክፍል የደጃዝማች ውቤ መቃብር ቤት ይገኛል፡፡ ደረስጌዎች ውለታ የማይረሱ ታሪክ አክባ ሪዎች ናቸው፡፡ የደጃዝማች ውቤን ዐፅም በሳጥን አስገብተው፣ መጎናፀፊያ አልብሰው በመቃብር ቤቱ አስቀምጠውታል፡፡ እኔን የገረመኝ እንደዚህ ዓይነት ሊጎበኝ የሚችል የታላላቅ ሰዎች የመቃብር ቦታ በደረስጌ መኖሩ ነው፡፡ ይህንን የመሰለውን አሠራር ያየሁት በአውሮፓ ነበረ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ምናልባት በኣታ የሚገኘው የዐፄ ምኒሊክ መቃብር ቤት ሊመስለው ይችል ይሆናል፡፡
የመቃብር ቤቱ ግድግዳው እና ጣራው በታሪካዊ ሥዕሎች የተሞላ ነው፡፡
*
የደረስጌ ማርያም የግድግዳ ላይ ሥዕሎች

 
*
           ደጃዝማች ውቤ ኃይለ ማርያም፤
              በደረስጌው ሰዓሊ ዓይን


ደጃዝማች ውቤ ቤተ ክርስቲያኗን ያሠሩት ከኖራ፣ ከድንጋይ እና ከጭቃ ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ እንደ ሚናገሩት ኖራው ሰባት ዓመት ይቀበራል፡፡ በየጊዜውም ውኃ ይጠጣል፡፡ በሰባት ዓመቱ ይወጣና ከጭቃው ጋር እየሆነ ድንጋዩ ይያያዝበታል፡፡ ከዚያ በኋላ ንቅንቅ የለም፡፡ ኖራው ተቀብሮ የቦካበት ቦታ ለታሪክ ዛሬም ድረስ ይታያል፡፡ ሲሚንቶ እንዲህ ተወድዶ ወገባችንን ከሚቆርጠን ምነው ይህንን ነባር ቴክኖሎጂ አዳብረን ብንጠቀምበት? ደጃዝማች ውቤ እንዴት ባለ ልዩ ውበት እንዳሠሯት አንደኛውን የዐፄ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል የጻፈው ወልደ ማርያም «ከባሕር ወዲህ እንደ እርሷ ድንቅ ተብሎ የሚነገር ሥራ የለም» ሏታል፡፡
*

የደጃች ውቤ መቃብር


 
አሁን ከቤተ መቅደሱ እንውጣ፡፡ በስተ ቀኛችን ወዳለው ዕቃ ቤትም እናምራ፡፡ 
kifle 3

ወደ ደረስጌ ማርያም ክፍል ሦስት

by Daniel Kibret on Tuesday, November 30, 2010 at 1:16pm
        የደረስጌ ዕቃ ቤት

                          የወርቅ ከበሮ

የደረስጌ ካህናት በአንድ ነገር ይመሰገናሉ፡፡ ደጃች ውቤ ከሰጡት ቅርስ እና ንዋያተ ቅድሳት መካከል አንድም እስካሁን አልጠፋም፡፡ በጣልያን ዘመን እንኳን ቤተ ክርስቲያንዋን ለመዝረፍ የመጣውን ጣልያን ቀጥታ ከዚህ በኋላ አልደርስም እነዲል አድርጋዋለች፡፡ በ1928 ዓም መጋቢት ሦስት ቀን ጣልያን በደብርዋ ላይ ያዘነበው የአውሮፕላን ቦንብ እንኳን እሳቱ ጢሱ አልነካትም፡፡


የቱሪዝም ቢሮ ባለሞያው አቶ አደራጀው እንደነገረን የደረስጌ ቅርስ ተሠፍሮ ተቆጥሮ በሚገባ የተመዘገበ ነው፡፡ በየዓመቱ ቆጠራ ይደረጋል፡፡ የሚገርመው ግን ቅርሱን ለመቁጠር ሁለት ወር ከአሥራ አምስት ቀን መፍጀቱ ነው፡፡ የአካባቢው ገበሬ ለቅርሱ ከፍተኛ ጥበቃ ነው የሚያደርገው፡፡ ዕቃ ቤቷ እና የያዘችው ዕቃ ሲተያዩ ወርቅን በቀዳዳ ኪስ እንደ ማስቀመጥ ነው፡፡ ከኖራ እና ከድንጋይ ተሠርታለች፡፡ ቅርሱ በቅርስ ላይ ተነባብሮ ተቀምጦባታል፡፡ በቅርቡ ደረጃውን የጠበቀ ሙዝየም ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ አደራጀው ነግሮኛል፡፡ ለማየት ያብቃን፡፡

                       የወርቅ ጽዋ
ደጃዝማች ውቤ ደረስጌ ማርያምን ሲሠሩ አንድ ምኞት ነበራቸው፡፡ ዘመነ መሳፍንትን አክትመው በደረስጌ ማርያም መንገሥ፡፡ ለዚህም አቡነ ሰላማን ከግብጽ አስመጥተው ነበር፡፡ እናም የተሟላ ንዋያተ ቅድሳት ለደብሯ አበርክተዋል፡፡ የብር እና የወርቅ ከበሮ፤ ከፋርስ እና ከግብጽ የመጡ ምንጣፎች፤ ከብር እና ከወርቅ የተሠሩ የፈረስ ኮርቻዎች፤ 70 ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያላቸው ከጎሽ ቀንድ የተሠሩ ዋንጫዎች፤ ለደብሯ ሰጥተ ዋታል፡፡

ይህም አልበቃቸው 483 ጋሻ መሬት ለቤተ ክርስቲያኑ ከመስጠታቸውም በላይ የአካባቢውን ገበሬዎች ከማንኛውም ግብር ነጻ አድርገዋቸው ነበር፡፡ የሰው ሃሳብ እና የእግዚአብሔር ሃሳብ ይለያያል፡፡ ደጃዝማች ውቤ እና ደጃዝማች ካሣ የካቲት ሦስት ቀን 1845 ዓም ቧሂት ላይ ጦርነት አደረጉ፡፡ ደጃዝማች ውቤም ተማረኩ፡፡ ቤቴል በሚባለው አምባ ላይም ያስቀመጡት ዕቃ ሁሉ ተማረከ፡፡ ዳጃዝማች ካሣም በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው በዚህችው በደረስጌ ማርያም የካቲት አምስት ቀን 1845ዓም ዐፄ ቴዎድሮስ ተብለው ነገሡ፡፡


ደጃዝማች ውቤ ሲማረኩ ዐፄ ቴዎድሮስ ሀብትዎን ያምጡ አሏቸው፡፡ ደጃች ውቤም «ይህንን ሁሉ ገንዘቤን ለእግዝትነ ማርያም መስጠቴ የምድር እና የሰማይ መከራ እንዳታሳየኝ ነበር፤ አሁን እንዴት ላድርግ ከእርሷ ይቀበሉ እንጂ፡፡» አሏቸው፡፡ የደጃች ውቤ ሠራዊትም እየሸሸ ደረስጌ ገብቶ ደወለ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም «ስለ እግዝትነ ማርያም ብዬ ምሬዋለሁ» ብለው ዐዋጅ ነገሩ፡፡

በልዩ ጌጥ የተሠራ መስቀል


   ከጎሽ ቀንድ የተሠራ ዋንጫ
 ምንም እንኳን ደጃች ውቤ በዚያ የመከራ ሰዓት አላዳነችኝም ብለው ቢፀፀቱም፤ ዐጽማቸውን አክብራ፣ታሪካቸውን አኑራ ትውልድ እንዲያስታውሳቸው ያደረገች፣ እስከ ዛሬም በጸሎተ ቅዳሴ እንዲታሰቡ ያደረገች ይህችው የደከሙላት ደረስጌ ማርያም ናት፡፡ የሰማዩንም እንደማትነሣቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አሁን ከዕቃ ቤቱ ወጥተን ወደ ግራ በኩል እናምራ፡፡
kifle 4

አንድ ጥንታዊ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ በዚህ ቦታ ይገኛል፡፡ ወደ ሕንፃው በደረጃ በኩል ትወጣላችሁ፡፡ ከከዚያም በደረጃ ወደ መጀመርያው ፎቅ ስትወጡ በፊት ለፊቱ በኩል በረንዳ ታገኛላችሁ፡፡ ወደ በረንዳው ዝለቁ፡፡

እነሆ አሁን የኢትዮጵያን ታሪክ በቀየረ አንድ ታሪካዊ ቦታ ላይ ቆማችኋል ማለት ነው፡፡ እዚህ ሠገነት ላይ ቆመው ነበር ዐፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን ያወጁት፡፡ የዘመነ መሳፍንት ማብቂያ እና ኢትዮጵያ ወደ አዲሱ ዘመን መሸጋገርዋ የታወጀው እዚህ ቦታ ላይ ነበር፡፡ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው ከዚህ ሠገነት ላይ ነው፡፡

ሠገነቱን ለቅቀን ካህናቱ በሰጡን መሰላል አማካይነት ወደ ላይኛው ፎቅ ወጣን፡፡ የፎቁ ወለል የሆነው እንጨት በዕድሜ ብዛት አርጅቶ ፈራርሷል፡፡ ለታሪክ ታድሎ ታሪኩን የሚረሳ እንደኛ ያለ ማነው፡፡ ይህንን የዘመናዊት ኢትዮጵያ መነሻ ሕንፃ መጠበቅ አቅቶን ይኼው ወለሉ እዚህ እና እዚያ ተለያይቷል፡፡
*
ዐፄ ቴዎድሮስ ንግሥናቸውን ያወጁበት ሠገነት


እንዳንወድቅ እየተጠነቀቅን ወደ ላይ ወጣን፡፡ ከአናቱ በተያያዘ ከባድ እና ረዥም ብረት የታሠሩ ሁለት ደወሎች አሉ፡፡ ትልቁ ደወል አሥራ አምስት የፈረስ ጉልበት አለው ይባላል፡፡ ይህንን ደወል ከጀርመን ያመጡት ዶክተር ዊልሔለም ሺምበር ናቸው፡፡ ደወሉ በአሁኑ ጊዜ በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ ይደወላል፡፡ ለኅዳር 21፣ ለኅዳር 25 ለመርቆሬዎስ በዓል እና ለጥር 21 ቀናት፡፡ በጥንት ዘመን ደወሉ ሲደወል ከደረስጌ በግምት 200 ኪሎ ሜትር እስከሚርቀው ወገራ ድረስ ይሰማ ነበር ይባላል፡፡

በትንሹ ደወል ላይ እኔ ለጊዜው ትርጉሙን ያላወቅኩት ጽሑፍ ተጽፏል፡፡ Aloysij Lucenti Funde Romae ይላል፡፡ እስኪ የምታውቁት ተርጉሙት፡፡ በትንሹ ደወል ዙርያ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ይነበባል louis Del A Strasbourg L’an 1848 faite par
*
           ትንሿ ደወል


ከደወሉ ሥር ያለው መቆሚያ እንጨት ቃቃቃ ይላል፡፡ በአንድ እጄ ደወሉ የታሠረበትን አግዳሚ፣ በሌላ እጄ ራሱን ደወሉን ይዤ በትልቁ ደወል ላይ በዙርያ የተጻፈውን ጽሑፍ ለማንበብ ሞከርኩ፡፡ ሙሉቀን ባትሪ ያበራል፡፡ እኔ በላዩ ላይ ያደራውን ሸረሪት እየጠረግኩ ጽሑፉን እመዘግባለሁ፡፡

አንድ እግሬ ተንጠለጠለ፡፡ ዝቅ ብዬ አየሁት፡፡ በጨለማው ውስጥ ወለሉ ይታኛል፡፡ ቄሰ ገበዙ «ተጠንቀቅ፤ አደገኛ ነው» ይላሉ ከሥር ሆነው፡፡ በተለይም በስተ ጀርባ ያለውን ጽሑፍ ለማንበብ የግድ እግሬን ለቅቄ ደወሉን በያዘው አግዳሚ ተንጠልጥዬ ማለፍ አለብኝ፡፡ ሙሉቀን እየደገፈኝ ተንጠላጠልኩ፡፡ ቃቃቃ፡፡

ተመስገን፡፡ በሰላም የወለል እንጨቱ ላይ እግሬ ዐረፈ፡፡ ግን እርሱም ቢሆን ቃቃቃ እያለ ምሬቱን አሰማ፡፡ «አትጠግኑን እና ስንፈርስ ዝም ብላችሁ እዩን» እያለን ይሆን አልኩ በልቤ፡፡ የደወሉ ውፍረት ወደ ሃያ ሳንቲ ሜትር ይጠጋል፡፡ ከአግዳሚው ጋር በሚገባ በብረት ታሥሯል፡፡ አግዳሚው ደግሞ ከግድግዳው ጋር ተጎዳኝቷል፡፡

ጽሑፉ እንዲህ ይላል In Honorem Dei AC Beatae Marae birginis Anno Domini MDCCXLIII

*
በትልቁ ደወሉ ላይ ያለው ጽሑፍ


ደወሉ ያለበት ሕንፃ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት አገልግሏል፡፡ አሁን ጥገና የሚያ ስፈልገው ይመስለኛል፡፡ እንጨቱ አንዳች ድጋፍ ካልተደረገለት አንድ ቀን እንዳይለቀው እፈራለሁ፡፡ የቅርስ ባለሞያዎች እዚህ ቦታ ላይ ዜግነታዊ እና ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

እንደምንም ከተንጠለጠልንበት ወረድን፡፡ መሰላሉን እየተቀባበልን፣ አንዳችን ለሌላችን እየደገፍን ወረድን፡፡

ደረስጌ ማርያምን እንዲህ በቀላ ጎብኝቶ መፈጸም አይቻልም፡፡ የሚነገሩ፣ የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ ብዙ ነገሮች አሏት፡፡ የሚገርማችሁ ቤተ ክርስቲያንዋን የሚጠብቃት ኃይለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ኢጣልያ ኢትዮጵያን እንደ ወረረ በ1928 ዓም መጋቢት 3 ቀን ለሦስት ሰዓታት ያህል በደረስጌ ማርያም ላይ የቦንብ ናዳ ከአውሮፕላን አወረደባት፡፡ አእንደ ሠለስቱ ደቂቅ ጢሱ እንኳን አልነካትም እነኳን እሳቱ፡፡

በዓመቱ የቦንብ ናዳውን ያዘዘው የጣልያን ጦር አዛዥ ወደ አካባቢው ሲመጣ በቤተ ክርስቲያንዋ ላይ ምንም እንዳልተከሰተ ያያል፡፡ «እኔ ዬስ ጉግሳ ቤተ መንግሥት መስሎኝ እንጂ እንዲህ ያለች ባለ ተአምር ቤተ ክርስቲያን መሆንዋን መቼ ዐወቅኩ» ብሎ ተፀፀተ ይባላል፡፡

*
            ትልቁ ደወል


ይህ ባለ ሥልጣን ከቤተ ክርስቲያንዋ ዐጸድ ለባንዴራ ማንጠልጠያ የሞሆን እንጨት ሊያስቆርጥ ሲነሣ ካህናቱ «ተው መቅሰፍት ይወርድብሃል፤ እንኳን ዛፏን ቆርጠው በአጠገቧ በበቅሎ አታሳልፍም» ይሉታል፡፡ እርሱ ግን የሚመጣውን አየዋለሁ ብሎ ማስቆረጥ ይጀም ራል፡፡ ወዲያው በግቢው ውስጥ በበቅሎ ሲያልፍ ከበቅሎው ወድቆ ተሰበረ፡፡ አጃቢዎቹ ወዲያው አፋፍሰው ወደ አንምድ ጥግ ሲወስዱት ሞተ፡፡

1930 ዓም ደግሞ ሌላው የጣልያን ጦር አዛዥ ለሞቱበት ወታደሮች በግቢው መቃብር ሊያስቆፍር ሲነሣ የደብሩ አለቃ እና ሽማግሌዎች ከለከሉት፡፡ በዚህ ተናድዶ ሕዝቡን እፈጃለሁ ብሎ ሲነሣ መብረቅ ሐምሌ 21 ቀን ወርዶ እርሱን እና ባንዴራውን ለይቶ መታው፡፡

ከደረስጌ ወጣሁ፡፡ የካህናቱ ትኅትና፣ የአቶ አደራጀው መስተንግዶ፣ ከኅሊናዬ አይጠፋም፡፡ አሁን የወረዳው መስተዳድር እና የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሙዝዬም ሠርቶ ቅርሱን ለመጠበቅ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ወደ ስሜን ተራሮች የሚመጡ ጐብኝዎች ሃምሳ ኪሎ ሜትር ብቻ ተጉዘው ሊያዩዋት ይችላሉ፡፡ ከጎንደር ደረስጌ ወደ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነው፡፡

ሙዝየሙን ለመሥራት ሁላችንም ብናግዛቸው የትውልድም፣ የሃይማኖትም ግዴታችንን ተወጣን ማለት ነው፡፡ ያለበለዚያ ባዶ ቁጭት ይሆንብናል፡፡ እኔ አበቃሁ፡፡ ወደ ጎንደር ልመለስ ነው፡፡ ሰላም ያግባን፡፡








Tuesday, November 9, 2010

do u know zozamba

This monastery found in north Gondar zone.it made before lalibela rock hewn church, and built by atse lalibela.
here is another